Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአዲሱ አመት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ- ከንቲባ ከድር ጁሃር 

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና የከተማዋን እድገት የሚያንፀባርቁ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ ሲሉ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ለ2015 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከንቲባው በመልዕክታቸው በመንግስት ምስረታ ወቅት ቃል በተገባው መሠረት የህዝቡ የቆዩ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን አመላክተዋል፡፡

በዚህም በ2014 በጀት ዓመት ከዚህ በፊት ተጀምረው ያልተጠናቀቁና በበጀት አመቱ ግንባታቸው ተጀምረው ከነበሩ የካፒታል በጀት ፕሮጀክቶች ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት መገኘቱንና የከተማዋን ፅዳትና ውበት ለማስጠበቅ በተከታታይ ለ48 ሳምንታት ያለማቋረጥ ህብረተሰብ አቀፍ የፅዳት ዘመቻ መካሄዱንም ጠቅሰዋል፡፡

በድሬዳዋ ከኢንዱስትሪና ከንግድ ማዕከልነቷ ጎን ለጎን ትላልቅ ሆስፒታሎች ግንባታ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል፡፡

ለመላው የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎችና ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የመልካም አዲስ ዓመት ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተሾመ ኃይሉ

Exit mobile version