Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶችን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል ስርዓት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ክፍያ የሚያስፈልጋቸውን የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል ስርዓት ተጀምሯል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሂሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ በኦንላይን የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶችን የክፍያ ስርዓታቸውን ከቴሌ ብር ጋር በማስተሳሳር የማስጀመሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የክፍያ ስርዓቱ ሳይቆራረጥ አገልግሎት እንዲሰጥ በቅንጅት ለመስራት ያስችላል መባሉን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሲራጅ ረሺድ እና የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ ተፈራርመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ እንደገለጹት÷ “በኦንላይን“ የሚሰጡ አገልግሎቶች የክፍያ ስርዓታቸው ከቴሌ ብር ጋር መያያዙ ዜጎች ክፍያ ለመፈፀም የሚገጥማቸውን እንግልት የሚቀርፍ ነው።

ስርዓቱ ዜጎች ካለምንም አድልኦ እና እንግልት በተቀላጠፈ ሁኔታ አገልግሎት እንዲያኙ በማስቻል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው÷ ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌ ብር የክፍያ ስርዓት ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው ከፍያ እንዲፈፅሙ በማስቻል የበርካታ ዜጎችን እንግልት ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

Exit mobile version