Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ2015 በጀት ዓመት ከቡና ምርት 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት ከቡና የውጪ ንግድ 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱ ተገለፀ፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 12 ቢሊየን ዶላር ከውጪ ንግድ የተገኘ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላሩ ከቡና የወጪ ንግድ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህም ጥሩ ስኬት ሲሆን ይህ ውጤት እንዲመዘገብ የአቅርቦት መጨመር አንዱ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

ይህን ስኬት ለማስቀጠልም የግብርና ሚኒስቴር፣ የቡናና ሻይ ባለስልጣንና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ እየሰሩ መሆኑ ታውቋል፡፡

በቡና ምርት የታየውን መነቃቃትም በሌሎች ምርቶች ላይ ለመድገም ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም የዓለም ገበያ የሚፈልገውን ጥራት እና መጠን ያማከለ ምርት እንዲኖር ሚኒስቴሩ እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው በ2015 በጀት ዓመት 360 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጪ በመላክ 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በበጀት አመቱ ከቡና በተጨማሪም ከወጪ ንግድ ከቅባትና ጥራጥሬ እህሎች 595 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷልም ነው ያሉት፡፡

በአጠቃላይ በ2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

Exit mobile version