Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህብረተሰቡ ዕኩይ አላማ ለማስፈፀም ከሚንቀሳቀሱ አካላት አካባቢውን ሊጠብቅ ይገባል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዕኩይ አላማ ለማስፈፀም ተልዕኮ ወስደው ከተማዋን ለማወክ ከሚፈልጉ አካላት ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ተደራጅቶ በንቃት አካባቢውን እንዲጠብቅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ለአዲስ አመት የእንኳን  አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ አዲሱ አመት ጥላቻ በፍቅር ተቀይሮ፣ መገፋፋት በመቀራረብ ተተክቶ፣ ጥርጣሬ በመተማመን ተቀይሮ፣ መከፋፈል በአንድነት  ተረቶ፣ ስንፍና በትጋት ተለውጦ የሚታይበት አመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ አመት “መከባበራችን መደማመጣችን የሚጠነክርበት፣ ድህነት በብልፅግና የሚቀየርበት፣ ያሰብነውን ያለምነውን፣ ያቀድነውን በላቀ ሁኔታ የምንፈፅምበት ይሁንልን” ሲሉም ነው መልካም ምኞታቸውን የገለጹት።

“ትብብራችን፤ አንድነታችን፤ መተሳሰባችን፣ በጎነታችን ይበልጥ የሚጎላበት”፤ የኢትዮጵያ ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ የሚሆንበት ይሆን ዘንድም ተመኝተዋል፡፡

የአዲስአበባ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ በዓሉን መሰረት በማድረግ ገበያው የተረጋጋ እንዲሆን የፍጆታ፣ የእንስሳትና የሰብል ምርቶችን በብዛት ወደ ከተማዋ እንዲገባ እያደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ በየእሁድ ገበያዎች እና በሸማች ማህበራት ሱቆች በመገኘት ግብይት እንዲፈፅምና በዓልን መሰረት አድርገው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ለሚያደርጉ አካላት ተጋላጭ እንዳይሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህን ለማረጋገጥም ለዚህ ስራ በተደራጀው ግብረሃይል አማካኝነት ጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

ማንኛውንም አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙ ለፖሊስና  በየአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ሃይል ፤ እንዲሁም ለመንግስት አስተዳደር በማሳወቅ በአሉ የፍቅር የሰላም የአብሮነት የመተሳሰብ በዓል እንዲሆን በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

 

 

 

 

Exit mobile version