አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓለም ዙሪያ 50 ሚሊየን ሰዎች “በዘመናዊ ባርነት” ውስጥ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰዎች በማይፈልጉት ሥራ፣ በግዴታ ጋብቻ እና በሌሎች ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ዓለም አቀፉ የሰራተኞች እና የፍልሰተኞች ድርጅት ያወጡትን የጥናት ውጤት ዋቢ አድርጎ ድርጅቱ ገልጿል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከፍላጎት ውጭ በማይወዱት ስራ ሲሰማሩ፥ ቀሪዎቹ ደግሞ በግዴታ ትዳር መስረተዋልም ነው ያለው የጥናቱ ውጤት።
በዚህ ስሌት መሰረት ዓለም ላይ ከ150 ሰዎች መካከል አንዱ “በዘመናዊ ባርነት” ውስጥ ይገኛልም ነው ያለው የድርጅቱ መረጃ።
የመንግስታቱ ድርጅት በፈረንጆቹ 2030 “ዘመናዊ ባርነትን” እና ለዚህ የሚዳርጉ ምክንያቶችን ለማጥፋት ግብ አስቀምጫለሁ ቢልም፥ ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2021 ብቻ በማይፈልጉት ስራ የተሰማሩ እና በግዳጅ ትዳር የመሰረቱ ሰዎች ቁጥር በ10 ሚሊየን መጨመሩንም ነው ጥናቱ ያመላከተው፡፡
ለዚህ ደግሞ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ግጭት እና ጦርነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዜጎች ዝቅተኛ ገቢ እና ፍልሰት በሰዎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠራቸው ምክንያት መሆኑም ነው የተጠቀሰው።
ዓለም አቀፉ የሰራተኛ ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ጋይ ራይደር በግዳጅ ስራ ላይ ትኩረታችንን ቀንሰናል ያሉ ሲሆን ፥ በምልመላና በሠራተኛ ቁጥጥር ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
የግዳጅ ሥራ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ችግር ብቻ ነው ብሎ ማመን ስህተት መሆኑን በመጥቀስም ፍልሰተኞች ከአካባቢው ነዋሪዎች ከሦስት እጥፍ በላይ ለችግሩ ተጋላጭ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ሴቶችና ህጻናት ተጋላጭነታቸው ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ እንደሆነ መገለጹን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በግዳጅ ስራ ካሉ አምስት ሰዎች መካከል አንዱ ህጻን ሲሆን ፥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በወሲብ ንግድ ውስጥ መሆናቸውን የጥናት ውጤቱ አመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

