አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል የ2015 ትምህርት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሁሉም አከባቢዎች ተካሄደ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል መሠረት ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ መንገዶችና ትራንስፖርት ልማት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ፥ የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ማስጀመሪያ መረሐ ግብር በጌዴኦ ዞን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።
”ትምህርት ለሁሉም ሁሉም ለትምህርት” በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ክልል የ2015 ትምህርት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በሁሉም አከባቢዎች እየተካሄደ እንደሚገኝም ኃላፊው ገልጸዋል።
የመማር -ማስተማር ሥራው ውጤታማ እንዲሆን የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ሁሉም የትምህርት ማህበረሰብ ወላጆች ፣ ተማሪዎች ፣ መምህራን ፣ ባለሃብቶችና አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በመርሐ ግብሩ ቢሮ ኃላፊውን ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ ፣ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴን ጨምሮ ከፍተኛ የዞን የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የትምህርት ማህበረሰብ በተገኙበት የ2015 ትምህርት ዘመን የመማር- ማስተማር ሂደት በይፋ መጀመሩን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል።