አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት ከጨርቃ ጨርቅ ምርት ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት መታቀዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
ዕቅዱን ለማሳካትም አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የጨርቃጨርቅ ኢንቨስትመንት ለማስተዋወቅ ያለመ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየዉ ኮንፈረንስ ÷ በኢትዮጵያ፣ ቻይና እና ጀርመን መካከል ያለውን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመደገፍና ለማበረታታት በጋራ የሚተገበር ፕሮጀክት መሆኑም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የጀመረችውን ሥራ ለማበረታታት፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ እና የኢንቨስትመንት አማራጮችንና መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ የኮንፈረንሱ ፋይዳ የጎላ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

