አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለፌዴራል ሥርዓቱ መጎልበት እና ለሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ተቋማዊ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ፡፡
ምክር ቤቱ ከፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በባሕርዳር ከተማ የስልጠና መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ፊስካል ፌዴራሊዝም በፌዴራልና ክልል መንግሥታት መካከል ያለው የወጪ ኃላፊነትና የገቢ ሥልጣን ክፍፍል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለፌዴራል ሥርዓቱ መጎልበት እና ለሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በበይነ መንግሥታት የፊስካል ግንኙነት ላይ ተቋማዊ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን ለመዘርጋት በብርቱ መሥራት ይገባል ብለዋል።
ከለውጡ በፊት የፊስካል ፌዴራሊዝም አፈፃፀም መልካም የሚባሉ ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደነበር የገለፁት አፈ ጉባኤው ከአሰራር እና ከአተገባበር ጋር ተያይዞ ግን በርካታ ችግሮች የተስተዋሉብት እንደነበር አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ምክር ቤቱ አሁን ላይ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ለጋሽና ደጋፊ አካላት ጋር በመተባበር ዘለቄታዊ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እየሠጠ የሚገኘው ይህ ስልጠና በተለያዩ ክልሎች ለአራተኛ ዙር እየተሰጠ እንደሚገኝ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

