አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ለሁለተኛ ጊዜ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 3 ሺህ 656 የእርድ እንስሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ክልሉ 1 ሺህ 411 ሰንጋ ፣ 1 ሺህ 85 ፍየል ፣ 1 ሺህ 160 በግ በድምሩ 3 ሺህ 656 የእርድ እንስሳት ነው ድጋፍ ያደረገው፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ መስከረም ደበበ ÷የሀገርን ህልውና ለሚያስጠብቀው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህዝቡ ደጀንነቱን እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስቴር የግዢ ዳይሬክተር ጄኔራል አለምሰገድ ወንዶሰን በበኩላቸው÷ ድጋፍ ያለው ሰራዊት ሁልጊዜም አሸናፊ መሆኑን ገልጸው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ11 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ 230 ሰንጋዎች፣ 52 በጎች፣ 22 ፍየሎች እና ሌሎች ምግብነክ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም በጥሬ ገንዘብ 2 ሚሊየን 85 ሺህ ብር ማበርከታቸውን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቅድስት ብርሃኑ እና ለሊሲ ተስፋዬ