Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሩስያ በተለያዩ የዩክሬን ግዛቶች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩስያ በተለያዩ የዩክሬን ግዛቶች በሚገኙ የዩክሬን ጦር ይዞታዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሩስያ ጦር ኃይሎች በኬርሶን፣ ሚኮላይቭ፣ ካርኪቭ እና ዶኔትስክ ክልሎች ጥቃት ማካሄዳቸውን ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው የጠቀሰው።

የዩክሬን ጦር በበኩሉ ኬርሶን በሚገኘው ፕራቭዳይን አቅራቢያ ያልተሳካ የማጥቃት ሙከራ ማድረጋቸውንም ጠቁሟል።

በተለይም ዛሬ በዛፖሬዥያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ አቅራቢያ ሁለት የዩክሬን የተኩስ ጥቃቶች መፈፀማቸውንና የተሰማውንም ስጋት ሚኒስቴሩ አመላክቷል።

ሆኖም በአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የሆነው ይህ ተቋም አሁን የሚያሳየው የጨረር ሁኔታ መደበኛ እንደሆነም ሚኒስቴሩ ጨምሮ አስታውቋል።

በሌላ በኩል የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፥ የዩክሬን ኃይሎች በተቋሙ አቅራቢያ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል በሩስያ በኩል የሚሰነዘረውን ክስ አስተባብለዋል።

ሩሲያ እና ዩክሬን በደቡባዊ ዩክሬን በሚገኘው የዛፖሬዥያ ኒውክሌር ኃይል ማመንጫ አቅራቢያ ተኩስ ተፈፅሟል በማለት እርስ በርሳቸው ደጋግመው ሲካሰሱ ቆይተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ኤጀን፥ሲ ሩሲያ በፋብሪካው ላይ ያላትን ወረራ እንድታቆም ከትናንት በስቲያ ውሳኔ ማሳለፉን ሬውተርስ ዘግቧል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዩክሬይን ተዋጊዎች በሩስያ ጦር ተይዘውባቸው የነበሩ ግዛቶችን ለማስለቀቅ የመልሶ ማጥቃት እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version