አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቻይና በታይዋን ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ሀገራቸው ታይዋንን እንደምትከላከል አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ባይደን ከሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ አሜሪካ ከታይዋን ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከምትከተለው ፖሊሲ ያፈነገጠ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጆ ባይደን ቻይና በታይዋን ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ አሜሪካ ታይዋንን ትከላከላለች ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “አዎ ትከላከላለች” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ የአሜሪካ ወታደሮች ታይዋንን ለመከላከል በቀጥታ የሚሳተፉ መሆኑን ነው ያረጋገጡት፡፡
የባይደንን ምላሽ ተከትሎም አሜሪካ በታይዋን ላይ የምታራምደው ፖሊሲ እና የአንድ ቻይና ፖሊሲ ማክበሯን አቁማለች በሚል ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡
ከባይደን አስተያየት ጋር ተያይዞ ኋይትሐውስ በሰጠው ማብራሪያ÷የአሜሪካ ፖሊስ እንዳልተቀየረ በማስረገጥ ከፕሬዚዳንቱ ምላሽ ጋር የሚቃረን ሃሳብ ሰጥቷል፡፡
በማብራሪያው አሜሪካ የአንድ ቻይና ፖሊስን እንደምታከብር እና ታይዋንን ጨምሮ ሁሉም የቻይና ግዛቶች በቤጂንግ እንደሚመሩ እውቅና ሰጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ ታይዋን ነጻ የመሆን እድሏን ራሷ ትወስናለች፤ አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት እንደማትቀሰቅስ፣ ነጻ ሀገር የመመስረቱን ሂዳት እንደማታበረታታ እና ውሳኔው የራሷ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ጆ ባይደን ከዚህ ቀደም ቤጂንግ በታይዋን ላይ ወታደራዊ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ አሜሪካ ታይዋንን ለመከላከል ዝግጁ እንደሆነች መናገራቸውን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር በታይዋን ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ በዋሺንግተን እና ቤጂንግ መካከል ያለው ውጥረት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡

