አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአገራችን ሚዲያዎች ተደራሽና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የውጭውን ሚዲያ ተሞክሮ እንዲያገኙ ለማስቻል እንዲሚሰሩ በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አልይ ገለፁ።
አምባሳደሩ ይህንን ያሉት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አመራሮች በኳታር ዶሃ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
የኢትዮጵያን ገፅታ ለማስተዋወቅ እና የዲፕሎማሲ ስራን ለመደገፍ የሚዲያ ስራ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ፈይሰል፥ ፋና በዚህ ረገድ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች እና የቱሪዝም መዳረሻዎች በማስተዋወቅ ሚዲያው የጎላ ድርሻ አለው ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
የአገራችንን የለውጥ ጉዞ ወዳጅ አገራት በውል እንዲረዱ እና ሁለንተናዊ እገዛ እንዲደርጉ ፋና እየተጫወተ ያለውን ሚና አድንቀዋል።
የመንግስትና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ እንዲጠናከር የሚዲያ ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑም ፋና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራውን ከሀገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር በመጣመር በስፋት ሊሄድበት ይገባልም ነው ያሉት።
ለአገራዊ ልዕልና መስራትን እና አሸናፊነትን ይበልጥ ለመጎናፀፍ እንደ አልጀዚራ ካሉ ተቋማት ልምድ መቀመርም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
የአገራችንን መልካም ገፅታ ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ለማድረስ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ፋና ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለም መድረኮች ሁሉ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ሊገነቡ ለሚችሉ መረጃዎች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት፡፡
የአገርን እና የህዝብን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ የሚሰሩ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

