Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አሸባሪው ህወሓት በአገዛዝ ዘመኑ የኦሮሞን ሕዝብ የመብት ጥያቄ ሲያፍን የነበረው ቁስል አልዳነም – የአባ ገዳዎች ሕብረት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአገዛዝ ዘመኑ የኦሮሞን ሕዝብ ሀብት ከመዝረፍ አልፎ የመብት ጥያቄ ሲያፍንና ሲገድል የነበረው ቁስል አልዳነም ሲሉ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ሕብረት ገለጹ።

የሕብረቱ አባላት እንደገለጹት÷ አሸባሪው ቡድን የኦሮሞ ሕዝብ በማንነቱ ቀና ብሎ እንዳይሄድና ባህሉን እንዳያሳድግ አድርጓል፡፡

በ2009 ዓ.ም በሆራ አርሰዲ በነበረው የኢሬቻ በዓል ለማክበር በተሰበሰበው ሕዝብ ላይ ጥቃት በመፈፀም ከአንድ ቤተሰብ እስከ አምስት የሚደርሱ ልጆች ያለቁበት ክስተት የሽብር ቡድኑ የጥፋት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ቡድኑ 27 ዓመት ሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በኦሮሞ ቄሮና ቀሬዎች ብሎም የኦሮሞ ምሁራን ላይ ይሄ ነው የማይባል ግፍ ፈጽሟ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የመሬት፣ የገንዘብና የንብረት ዝርፊያ ሲፈጽም መኖሩንም ነው የተናገሩት፡፡

የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ከስልጣን እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ በሕዝብ እና ሀገር ላይ ከፍተኛ በደል ማድረሱንም ገልጸዋል፡፡

አሻባሪው ህወሓት ወደ ስልጣን ሲመጣ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አስቦ ሳይሆን የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ መሆኑን ገልጸው÷ የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ጋር ቢኖር ይሻለዋል ብለዋል፡፡

ምክንያቱም አሸባሪው ቡድን ሕዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰደው መሆኑንም አስረድተዋል።

የትግራይ ህዝብ ለጥቂት ግለሰቦችና ቡድን ጥቅም ሲባል ልጆቹን ያልተፈለገ ዋጋ ማስከፈል እንደሌለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ሰላም የነሳንን አሸባሪ ቡድን እናወግዛለን ያሉት የኦሮሞ አባገዳ ሕብረት አባላት÷ የሰላም ጠል በመሆን ጦርነት መክፈቱን ለውጪው ማህበረሰብ ማስገንዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት በመጠቆምም÷ የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ብቸኛ ሀገሩን በአንድነት መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version