Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ችግር እንዳይገጥማቸው በትኩረት እየተሠራ ነው- የሱዳን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ችግር እንዳይገጥማቸው በሀገሪቱ መሪዎች ጭምር ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ተባብሮና ተመካክሮ ችግሮችን ለመቅረፍ ዝግጁ መሆናቸውን የሱዳን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሱዳን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሌተናል ጄኔራል አናን ሃሚድ ሞሃመድ ኦማር እና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር ያሉ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ይበልጣል በሱዳን የሚኖር ማንኛውም የውጭ ዜጋ ሕጋዊ ሆኖ መኖር የሚጠበቅበት ቢሆንም÷ በሱዳን የሚገኙ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ግን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ፣ ለመኖሪያና ሥራ ፈቃድ እንዲሁም ለመውጫ ቪዛ የሚጠየቀውን ክፍያ ለመፈጸም አቅም የሌላቸው፣ የመጓጓዣ ሰነድም ያልያዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም የሱዳን መንግሥት እነዚህን ወገኖቻችንን በልዩ ሁኔታ እንዲያስተናግዱልን፣ ከዚህ አኳያ ፓስፖርት እስከሚያወጡና የመኖሪያ ፈቃድ እስከሚይዙ እንዲታገሰን እና ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚሹትም የመውጫ ቪዛ ክፍያው እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።

ሌተናል ጄኔራል አናን ሃሚድ ሞሃመድ ኦማር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያውያን የሚገኙበትን ሁኔታ እንደሚረዱ እና በቀረበው ጥያቄ መሰረት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ተባብረው ለመሥራት ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ለዚህም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ጉዳዩን የሚከታተል እና ከኤምባሲው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር ተመካክሮ የሚሰራ ኃላፊ ወክለዋል።

ኢትዮጵያውያን ችግር እንዳይገጥማቸው በሀገሪቱ መሪዎች ጭምር ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ተባብሮና ተመካክሮ ችግሮችን ለመቅረፍ ዝግጁ ነን ሲሉ ማረጋገጣቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version