Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል የተሰጠው የኢንቨስትመንት ፍቃድ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ስኬታማ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የተሰጠው የኢንቨስትመንት ፍቃድ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ስኬታማ መሆኑን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ተሾመ አዱኛ ፥ የኦሮሚያ ክልል በ2014 በጀት ዓመት 3 ሺህ 588 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፍቃድ መስጠቱን አንስተዋል፡፡

በዚህም የኢንቨስትመንት ፍቃድ እየተሰራ ያለው ሥራ የሀገርን ኢኮኖሚ በማሳደግና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ  ስኬታማ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ኃላፊው ይህን የገለጹት፥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ካፒታል ይዞ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና ንግድ ዘርፎች በመስራት በዓመት 57 ሚሊየን ብር የገቢ ግብር እያስገባ ያለው አርፋሳ ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰን የግል ማህበር 9ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ባከረበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው።

በዘርፉ ለተመዘገበው ስኬት አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኘውን አርፋሳ የግል ማህበርን አመስግነዋል የቢሮ ኃላፊው፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን እድገት የሚያግዙና ስራ አጥነትን በመቅረፍ ረገድ በክልሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች የተሰማሩ ባለሃብቶች ሚና ጉልህ በመሆኑ መንግስት በሚፈለገው ልክ ከጎናቸው ለመቆም ዝግጁ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ደገፋ ስሜ ፥ ድርጅታቸው የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውት ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንና ወደፊት ለያዘው ሰፊ ኢንቨስትመንት የክልሎችና የፌዴራል መንግስቱ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

አርፋሳ ጠቅላላ የንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በቡና ዘርፍ 30 ሚሊየን ዶላር ገቢ በማስገባት  የዓመቱ ምርጥ የሜዳሊያ  ተሸላሚ መሆኑ ይታወሳል።

በምናለ ገበየሁ

Exit mobile version