Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ወ/ሮ ሙፈሪሃት እና ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተመራ ልዑካን ቡድን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ጋር በስራ እድል ፈጠራና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

በውይይት መድረኩ በስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል የውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል፡፡

ወይዘሮ ሙፈሪሃት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አደረጃጀትና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በስራ እድል ፈጠራና የስልጠና ማዕከላት ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን እና የስራ ፈጣሪነትን ለሚያዳብሩ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችን አብራርተዋል፡፡

በየዓመቱ ከ2 ሚሊየን በላይ ሰልጣኞች በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ውስጥ እንደሚያልፉ ጠቁመው÷ይህን የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የእድል በር አድርጎ ለመጠቀም ስርዓተ ስልጠናውን ማስተካከል እንደሚገባ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ስራ ከስልጠና በላይ እንዲሆን ታስቦ እየተሰራ መሆኑ እና ተቋማቱ ሀሳብ ወደ ተግባር የሚተረጎምባቸው የቢዝነስ ሀሳብ ማበልጸጊያ እንዲሆኑ ይሰራል ተብሏል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ተቋማትም ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም በሚያስችሉ አዳዲስ የሙያ መስኮችን ማሰልጠን እንዲጀምሩ ይደረጋል ነው የተባለው።

ሰልጣኞች በስልጠና ተቋማት ውስጥ እያሉ ከስልጠናው ጎን ለጎን የኢንተርፕራይዝ የቢዝነስ ሀሳብ እንዲያመነጩና ወደ ተግባር እንዲገቡ እንደሚደረግና ተወዳዳሪ ምርጥ ሀሳብ ለሚያቀርቡም የአጋር አካላት ድጋፍ እንደሚመቻች ነው የተጠቆመው፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር እያደረገ ያለውን ተቋማዊ ለውጥ እና ይህን ተከትሎ የተደረጉ ማሻሻያዎች ማድነቃቸውን ከርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version