Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አሸባሪው ህወሓትን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለን ለመታገል ዝግጁ ነን – በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድንን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለን ለመታገል ዝግጁ ነን ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የማህበረሰብ ተወካዮች ተናገሩ፡፡

አሸባሪው ህወሓትን ማገዝ የትግራይ ሕዝብ ስቃይ እንዲራዘምና የትግራይ ወጣት አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዲከፍል ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የማህበረሰብ ተወካዮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

 

ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣትም የህወሓት ሽብር ቡድንን ያወገዙ ሲሆን÷ የጥፋት ቡድኑ በቃህ ሊባል እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

 

የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪው ህወሓት ያተረፈው ችግርና መከራ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው÷ ሕዝቡ መሰረታዊ አገልግሎት እንዳያገኝ ማድረጉን አንስተዋል።

 

አሸባሪው ህወሓት ክልሉን በመራበት ዘመንም አመራሮቹ በወረዳና በዞን ተከፋፍለው አገር ሲዘርፉ፣ ሕዝቡን ሲያሰቃዩ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

የትግራይ ተወላጆች ከመንግሥት ጎን ሆነው አሸባሪውን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት መታገል እንዳለባቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ሁሪያ አሊና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ያስሚን ወሀብረቢ እንደገለጹት÷ አሸባሪው ህወሓት አሁንም የትግራይ ሕዝብ ከመከራና ስቃይ እንዳይወጣ መንግስት የዘረጋውን የሰላም መንገድ መግፋቱና ለሕዝቡ ምንም ቦታ እንደሌለው ማሳያ ነው።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ኃላፊ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው÷ የትግራይ ተወላጆች የመንግስትን ጥረት መደገፍ እንዳለባቸውና አሸባሪ ቡድኑ ችግር የሚፈጥረው በተልዕኮ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version