አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር ለ4ኛ ዙር የፌዴራል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የዕውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
በምስጋና መርሐ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴን፣ ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።
በመርሐ ግብሩ 400 ለሚሆኑ የፌደራል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች ዕውቅና እና ሽልማት እንደሚሰጥ ነው ሚኒስረቴሩ ያስታወቀው፡፡
የእውቅና አሰጣጡ የገቢ አስተዋጽኦ ፣ የሕግ ተገዢነት፣ ወቅታዊ የስጋት ታሪክ ፣ የጉምሩክ ጥፋት አይነት፣ የደህንነትና የወንጀል ሪከርድ እንዲሁም ሌሎች መስፈርቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ ድርጅቶችና ግለሰቦችም የወርቅ፣ የፕላቲኒየም እና የብር ደረጃ ሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ336 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል፡፡
ሚኒስቴሩ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ታክስ እና ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ አገልግሎት 450 ነጥብ 29 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

