አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የፓርቲም ሆነ የመንግሥት ስብሰባዎች እንዲቆሙ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ወሰነ።
ኮማንድ ፖስቱ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ ከነገ ጀምሮ በክልሉ የፓርቲም ሆነ የመንግስት ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ መወሰኑን አስታውቋል።
ከዚህ ባለፈም የመዝናኛ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች እንዲዘጉ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ፣ ሰርግን ጨምሮ ተያያዥ ማህበራዊ ግንኙነቶች እንዲቆሙ እና የተሽከርካሪ ባለቤቶች ከመደበኛ የመጫን ልካቸው በግማሽ እንዲቀንሱም ውሳኔ አሳልፏል።
በተጨማሪም ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮችን በመቀነስ፥ ወደ ግብይት ማዕከላት አዘውትሮ አለመሄድ፣ ከኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ጋር ከተያያዘ ስምሪት ውጭ የሠራተኞች የመስክ ስምሪት እንዲቆም፣ ህብረተሰቡ ከቦታ ቦታ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲቀንስም ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።
ኮማንድ ፖስቱ በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።
በክልሉ አጎራባች አካባቢዎችና የሱዳን ድንበር የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲደረግ፣ ሁሉም ተቋማት የሠራተኞቻቸውን ደህንነት እንዲጠብቁ እና የመከላከያ ቁሳቁስ እንዲያሟሉ የፀጥታ ኃይሎች የሚሰጣቸውን ስምሪት በብቃት እንዲወጡ ውሳኔ ማሳለፉንም ነው ያስታወቀው።
ወደ ሃይማኖት ተቋማት ለመሄድም ጤና ሚኒስቴር ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ መከተል እንደሚገባም ኮማንድ ፖስቱ አሳስቧል።
በናትናኤል ጥጋቡ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

