አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2015፣ (ኤፍ ቢ ሲ) የሸገር ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት በ50 ጥንዶች የሰርግ ስነስርዓት ታጅቦ እንደሚመረቅ ዛሬ ከተያዘው መርሐ ግብር ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ አበባን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እና ለስሟ የሚመጥን ገጽታ እንዲኖራት ታልሞ ሲሠራ የቆየው የሸገር ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት በስኬት መጠናቀቁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጹ የሚታወስ ነው።
ይህ ሥፍራ ለሀገር ኩራት፣ ለጎብኚዎች መዳረሻ፣ ለመዲናዋ ነዋሪዎች የዘወትር መገልገያ እንዲሆን መዘጋጀቱም ነው የተመላከተው።
የሸገር ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት መጠናቀቁን በማስመልከትም፥ ለምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ልዩ ስጦታ መዘጋጀቱን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የሸገር ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት የተለያዩ የሕፃናት መዝናኛዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የኪነጥበብ ዝግጅት ማሳያዎችን ይዟል።
በተጨማሪ የተለያዩ ሁነቶች የሚስተናገዱባቸውን ዘመናዊ አዳራሾችንና ማዕከላትን የያዘ መሆኑ ታውቋል።
የሸገር ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ ሕፃናት ባህልና ታሪካቸውን እያወቁ የተለያዩ ዕውቀቶችን የሚቀስሙበት የሕፃናት ማዕከልም ተገንብቶለታል።
ፓርኩ የሚገኝበት ስፍራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ፊት ለፊት አንስቶ ወደ አሮጌው ቄራ መውረጃና እሪበከንቱ ቁልቁለቱን የሚገኙ አካባቢዎችን ያጠቃለለ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ጽህፈት ቤቱ ጋብቻቸውን ለመፈጸም የተዘጋጁ ወይም አቅደው ሳይሳካላቸው የቆዩ 50 ጥንዶችን በመሥፈርት መርጦ የጋብቻ ሥርዓታቸውን በዛሬው ዕለት የወዳጅነት የሠርግ ዐጸድ እንዲፈጽሙ ማቀዱም የሚታወስ ነው።

