Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረጉ ሂደት በውስን የውጭ ባንኮች ብቻ እንደሚጀምር ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረጉ ሂደት ውስን ቁጥር ባላቸው የውጭ ባንኮች ብቻ የሚጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ እንደገለጹት÷ የውጭ ባንኮች ይዘውት የሚመጡት ካፒታል በኢትዮጵያ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለል ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

መንግስት በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፍ ለመሳተፍ የሚመጡ የውጭ ባንኮችን በሙሉ ተቀብሎ ፈቃድ እንደማይሰጥ ጠቁመው÷ ለመነሻነት ውስን የውጭ ባንኮችን ብቻ እንደሚያስተናግድ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም አራት ቅድመ ሁኔታዎች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡

ፈቃድ ማግኘት የሚችሉት በኢትዮጵያ ንዑስ ባንክና ቅርንጫፍ ለማቋቋም የሚጠይቁና ከሀገር ውስጥ ባንኮች እስከ 40 በመቶ አክሲዮን የሚገዙ የውጭ ባንኮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከአገልግሎት አንኳያም÷ በተለይ ለግብርና፣ ለቤትና ሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም ለገጠር አካባቢዎች የተለያዩ አገልግሎት ለመስጠት አልመው የሚመጡ ባንኮች የሚኖራቸው ፋይዳ ጉልህ እንደሚሆን ተናግረዋል።

አራቱን ቅድመ ሁኔታዎች ያሟሉ የውጭ ባንኮች ኢንቨስት ለማድረግ ከገቡ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ባንኮች መልካም እድል ይዘው እንደሚመጡት ሁሉ ስጋቶች እንደሚኖሩ አመላክተው÷ ስጋቶችን ለመቀነስ በዘርፉ ያለው ልምድ እየዳበረ እስከሚሄድ ድረስ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ባንኮችን ቁጥር በመገደብና አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የሚያደርገውን አሠራር እውን ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version