አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተከናውኗል፡፡
መርሐ ግብሩ “አዲስ አበባ ህብረ-ብሔራዊት የሰላም እና የፍቅር ከተማ” በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው፡፡
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅ/ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ÷ስፖርት የግል ጤናን ከመጠበቅ ባሻገር ለሰላም ያለው አስተዋጽኦ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ጤናችንን እየጠበቅን የከተማችንን ሰላምና ልማት አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል፡፡
በቤተሰብ ደረጃ የተጀመረውን “የሌማት ትሩፋት” ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ 2ኛ ዙር የ90 ቀን ልዩ እቅድ ይፋ ማደረጉን ያስታወሱት አቶ መለሰ÷ እቅዱ ከመደበኛ ስራዎቻችን ባሻገር ለብልጽግና ጉዞ ለምናደርገው ጥረት ልማታችንን የሚያፋጥን ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ፕሮግራም በዛሬው ዕለት በአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በይፋ መጀመሩንም አብስረዋል።
መርሐ ግብሩን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን÷ በቀጣይም በሌሎች ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መጠቆሙንም የከተማዋ ኮሙኒኬሽን
መረጃ ያመላክታል፡፡

