Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተሰረዘው የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ነገ እንደሚወጣ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ በተፈጸመ የማጭበርበር ወንጀል ምክንያት ተሰርዞ የነበረው የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ በነገው ዕለት እንደሚወጣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡
 
በጉዳዩ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ ያስሚን ወሀቢረቢና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሽመልስ ታምራት መግለጫ ሰጥተዋል።
 
በመግለጫቸውም በነገው ዕለት 25 ሺህ 791 የ40/60 እና 20/80 ቤቶች ዕጣ እንደሚወጣባቸው ተናግረዋል፡፡
 
በነገው እጣ 146 ሺህ 892 እስከ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በቂ ቁጠባ ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ነው የተባለው።
 
በነገው እጣ አወጣጥ ነባርና በ2005 ዓ.ም በባለሶስት መኝታ ቤት የተሰሩ 300 ቤቶችም ይተላለፋሉ።
 
በእጣ አወጣጡ ላይ ከዚህ ቀደም የገጠሙ ችግሮች እንዳይደገሙ አዲስ የእጣ አወጣጥ ስርዓት መዘርጋቱንም ነው ሀላፊዎቹ የተናገሩት።
 
የመረጃ ማጥራት እና ማደራጀት ስርዓቱ ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ መከናወኑም በመግለጫው ተነስቷል፡፡
 
የእጣ ማውጫ መተግበሪያውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ያለማው ሲሆን÷ከፌደራል ተቋማት እና ከከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች መሳተፋቸውም ተገልጿል፡፡
 
የእጣ አወጣጡ በቆጣቢዎች የቅድመ ግምገማ ወይም የእጣ አወጣጥ ሙከራ የተካሄደበት መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
 
ነገ ከሰዓት የሚካሄደው የእጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓቱም በቴሌቪዠን በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
 
በአፈወርቅ እያዩ
Exit mobile version