አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ሀሰተኛ መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ መንገስት ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ።
አቶ ንጉስ ጥላሁን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች አስመልክተው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥መንግስት በቫይረሱ ዙሪያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን በተገቢው ሁኔታ ለማህበረሰብ እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ግለሰቦች ከኢትዮጵዊነት ባህል ባፈነገጠ መልኩ ዜጎችን የሚያደናግሩ እና ለከፍተኛ ጉዳት የሚዳርጉ አሳሳች መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች እያሰራጩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆን ተብለው እና ታቅድው ህብረተሰቡን ለከፋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ቀውስ የሚዳርጉ መሰል መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል በተገቢው ስዓትና ጊዜ ይፋ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ መንግስት ካወጣቸው መረጃዎች ውጭ ምንም አይነት የተደበቀ መረጃ አለመኖሩን ያነሱት አቶ ንጉሱ፥ ከነባራዊ እውነታው ባፈነገጠ መልኩ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በመላኩ ገድፍ