አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
የሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ 87 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሶስት ተጨማሪ ሰዎች መገኘታቸውን አስታውቋል።
ይህንንም ተከትሎ በአጠቃላይ በሀገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 19 ደርሷል፡፡
የመጀመሪያዋ ታማሚ የ26 ዓመት ኢትዮጵያዊ ስትሆን መጋቢት 8፣ 2012 ከብራሰልስ ቤልጅየም እንዲሁም መጋቢት 10፣2012 ዓ.ም ወደ ካሜሮን የጉዞ ታሪክ የነበራት ሲሆን ግለሰቧ የበሽታው ምልክት ስለታየባት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ አድርጋለች፡፡
ተቋሙም ለኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖርት በማደረጉ በተደረገላት የላብራቶሪ ምርመራ በመጋቢት 19፣2012 ዓ.ም በቫይረሱ መያዟ ተረጋግጧል፡፡
ሁለተኛ እና ሶስተኛ ታማሚዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የ14 እና የ48 ዓመት የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
ግለሰቦቹ የበሽታውን ምልክት ባያሳዩም ከዚህ በፊት በቫይረሱ ከተያዘ ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ ስለነበራቸው በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ነበር፡፡ በመጋቢት 19 በተደረገላቸው የላቦራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

