አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩፍኝ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፊታችን ታህሣስ 13 ቀን ጀምሮ የሚሰጥ በመሆኑ እስከ 5 ዓመት የእድሜ ክልል ያሉ ህፃናት እንዲከተቡ ጥሪ ቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኩፍኝ በሽታ መድኃኒት ክትባት ማሠራጨቱን በመድኃኒት ክምችት አያያዝ አስተዳደር የክትባት መድኃኒት ተጠሪ አቶ ሀብታሙ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡
የክትባት መድኃኒቱ በመላው የኢትዮጵያ ክልሎች የሚካሄድ ሲሆን ፥ በዚህም 16 ሚሊየን 298 ሺህ በላይ ሕፃናትን መከተብ እንደሚል ተጠቁሟል፡፡
ክትባቱ ከታህሣስ 13 ቀን ጀምሮ እንደሚሠጥና እስከ 5 ዓመት የእድሜ ክልል ያሉ ህፃናት እንዲከተቡ ጥሪ መቅረቡን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኩፍኝ በሽታ በትንፋሽ ከሠው ወደ ሠው በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፍ ነው፡፡
ይህ በሽታም ሕፃናትን እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል በመሆኑ ማህበረሠቡ ይህንን በመገንዘብ ሕፃናቱን በወቅቱ እንዲያስከትብ አገልግሎቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

