Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአሜሪካ ቆይታ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም ያሳደገ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአሜሪካ የነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵንያ የዲፕሎማሲ አቅም ያሳደገ እንደነበር የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሜሪካ ቆይታቸው፥ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የሀገራት መሪዎች እና የአሜሪካ ሴናተሮች ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሰላምን ለማምጣት የወሰደው እርምጃ እውቅና ያገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፥ በተለይ ለስምምነቱ ትግበራ ያሳየው ቁርጠኝነት አድናቆት እንደተቸረው አስረድተዋል።

አሜሪካና ኢትዮጵያ በጋራ የሚሰሯቸውን የልማትና ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን አጠናክረው ለማስቀጠል መስማማታቸውንና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ ቀደመው ለመመለስ እንደሚሰራም አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ያካሄደችው የችግኝ ተከላ መርሐግብር እና ወደ ሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለማስፋት የምታደርገው ጥረት እውቅና እንዳገኘም ነው የገለጹት።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለመልሶ ግንባታ የምታደርገውን ጥረት ዓለም አቀፍ ድጋፎች የተገኘበት እንዲሁም ለቀጣይ ድጋፎችም መሰረት የተጣለበት ቆይታ መሆኑንም አመላክተዋል።

 

 

Exit mobile version