አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህፃናትን ከባድ ከሆነ በሽታ ለመከላከል ክትባት ቀላሉ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዘዴ በመሆኑ ወላጆች በወቅቱ እንዲያስከትቧቸው ይመከራል፡፡
ክትባት ለአንድ ለሚተላለፍ በሽታ መከላከያነት አስቀድሞ የሚወሰድ መድሀኒት ሲሆን÷ የሰውን በሽታ የመከላከል አቅም በማዳበርና የመከላከያ ኬሚካሎች እንዲያመርት በማድረግ በሽታን ከመምጣቱ በፊት ይከላከላል፡፡
ክትባቶች በአመት በርካታ ሰዎች በበሽታ እንዳይያዙ ሲከላከል በበሽታው የተያዙ ሰዎች በአካባቢው ቢኖሩ እንኳን ወደ ሰውነት ዘልቆ ገብቶ በሽታ እንዳይፈጠር ያደርጋል፡፡
ክትባት ከሚከላከላቸው የህፃናት በሽታዎች ውስጥ፡-
ዲፕቴሪያ ፡-ይህ በሽታ ወፍራም ፈሳሽ ጉሮሮ ውስጥ በማከማቸትና ሳንባን በማፈን እንዲሁም መተንፈስን በመከልከል የሚያጠቃ ካልታከሙ በቀር ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡
መንጋጋ ቆልፍ፡- የሰውነትን ጡንቻ በተለይ የመንጋጋ አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን በማጠንከር መተንፈስ እንዲከብዳቸው ያደርጋል፡፡
ትክትክ፦ በጣም ከባድ የሆነ የማያቋርጥ ሀይለኛ ሳል፣ ማስመለስ፣ መተንፈስ እስከሚከብድ ድረስ ሲኖር ትክትክ በሽታ ህፃኑ ሊኖርበት ይችላል፡፡
ኩፍኝ /ጆሮ ደግፍ፡- ኩፍኝና ጆሮ ደግፍ በቫይረስ የሚመጡ በሽታዎች ሲሆኑ የሰውነት ላይ ሽፍታዎችና ማሳከክ ሊኖር ይችላል፡፡
አንገት ስር በግራና በቀኝ ከትኩሳትና ከህመም ጋር የተያያዘ እብጠት ሲኖር ደግሞ የጆሮ ደግፍ ምልክቶች ናቸው፡፡
እነዚህ በሽታዎች ብዙ ጊዜ ለህይወት የሚያሰጉ በሽታዎች ባይሆኑም ህፃናቶችን እንዲሁም ትንንሽ ልጆችን ያሰቃያሉ፡፡
የህፃናት የሳንባ ምች ፡-አንድ ህፃን በተለይ ከ5 አመት በታች ሆኖ ራስ ምታት፣ ሳልና የአተነፋፈስ ችግር ካለበት በሳንባ ምች በሽታ ተይዞ ሊሆን ይችላል።
ይህንን አደገኛ በሽታ ለመከላከል የሚጠቅሙ ክትባቶችን ገና በልጅነቱ ካገኘ ግን ከእነዚህ በሽታዎች ይጠበቃል፡፡
ሄፐታይተስ ፡-የአይን ወይም የሰውነት ቢጫ መሆንና ተቅማጥ፣ ማስመለስ፣ መደካከም የጡንቻዎች፣ የመገጣጠሚያ ወይም ሆድ ህመም የሄፐታይተስ በሽታ በህፃናት ሲከሰቱ ከምናያቸው ምልክቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ፖሊዮ ፡-ይህ በሽታ በተለይም በሶስተኛ ዓለም ሀገራት የእግር አፈጣጠር ችግር ከሚያመጡ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን÷ በክትባት መከላከል የሚቻል መሆኑን ከጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ገፅ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

