Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከሁለት ኮከብና በላይ ባለ ማዕረግ ጄኔራል መኮንኖች በመዲናዋ የቤት መስሪያ ቦታ እጣ የማውጣት ስነ ስርዓት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለበርካታ ዓመታት ሀገራቸውን እና ህዝባችውን በታማኝነትና በጀግንነት ላገለገሉ ከሁለት ኮከብ እና በላይ ለሆኑ ባለ ማዕረግ ጄኔራል መኮንኖች በአዲስ አበባ ከተማ የቤት መስሪያ ቦታ እጣ የማውጣት ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡
 
የግንባታ ሂደቱም በባለእድለኛውና በመከላከያ ሚኒስቴር በወጪ መጋራት መመሪያና አሰራር መሰረት የሚፈፀም መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
 
በቀጣይ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም የተቀሩትን ባለ አንድ ኮከብ ጀነራሎችና ሲንየር ኮለኔሎች የመኖርያ ቤት ባለቤት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
 
መርሐ ግብሩ ሲፈፀም ከከፍተኛ ኮሎኔል ማእረግ ጀምሮ ወደላይ ያሉ የሰራዊቱን አባላት ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ አሰራር ነው ብለዋል።
 
ከዚህ በተጨማሪም ለሁሉም የሰራዊቱ መኮንኖችና አባላት የመኖርያ ቤት ችግርን የሚቀርፉ የድጋፍ ፕሮግራሞችን አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሉ በየደረጃው በተሻለ ፍጥነት እና አግባብ እንዲተገበሩ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
 
ይህንንም በስፋት የምንቀጥልበት ይሆናል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ሀገር ባላት አቅምና ኃብት ባለውለታዎችዋን ልታከብርና ልታመሰግን ይገባታል ብለዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ይህንን ፕሮግራም እንዲሳካ የሚያስፈልገው መሬት በማዘጋጀት ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
 
Exit mobile version