Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በተለያዩ አካባቢዎች በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሔደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና በወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ነው።
ውይይቶቹ በአዳማ፣ አሶሳ እና ሸገር ከተማ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በአዳማ ከተማ “ህብረ – ብሔራዊ ወንድማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪቃል እየተካሔደ የሚገኘውን የውይይት መድረክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ መርተውታል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር መንግስት ፅንፈኝነት፣ የኑሮ ውድነት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ውስጣዊ አንድነትን እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ከምንጊዜውም በላይ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
መንግስት የተደራጀ ሌብነትን ለመከላከል ህብረተሰቡን በማሳተፍ እያከናወነ የሚገኘውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ እየተካሄደ ያለውን ውይይት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ እና የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ መርተውታል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በወቅቱ እንዳሉት፥ በክልሉ ሀገራዊ ለውጡ ካስገኛቸው ውጤቶች አንዱና ዋነኛው የክልሉ ህዝቦች በሃገራዊ ጉዳዮች እኩል መሳተፋቸው ነው።
የክልሉ መንግስት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ የልማት እና መልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡ ውጤቶች የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከሩን በዋነኛነት ጠቁመዋል።
በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን በማንሳትም በሁሉም ዘርፍ ዜጎችን በማወያየት ማስቀጠል በመንግስት ትኩረት እንደተሰጠው አስረድተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ የክልሉ ህዝብ መከላከያን በስንቅና በትጥቅ በመደገፍ ላደረገው ተሳትፎ አመስግነዋል።
በሌላ በኩል በሸገር ከተማ በሚካሄደው ውይይት ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ፣ የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ።
ከሸገር ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች በመድረኩ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።
በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው ህዝባዊ ውይይት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሆሳዕና ከተማም እየተካሄደ ነው።
መንግስት የአንድን ሀገር ልማትና እድገት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የህዝብ አበርክቶ ትልቅ ድርሻ እንዳለው በመድረኩ ተገልጿል።
Exit mobile version