Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በተለያዩ የደቡብ ክልል ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የህዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የደቡብ ክልል ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የህዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት እየተከናወነ ነው ፡፡

ሕዝበ ውሳኔው በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በዛሬው ዕለት እየተካሄደ የሚገኘው የሕዝበ ውሣኔ ድምፅ አሰጣጥ ሒደት በደቡብ ኦሞ ዞን ባሉ 428 የምርጫ ጣቢያዎች መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በጂንካ ምርጫ ክልል ስር የሚገኙ 24 የምርጫ ጣቢያዎችም መራጮች ድምጻቸውን በመስጠት ላይ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ÷ በጂንካ ምርጫ ክልል አርክሻ ለ ንዑስ የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ሰጥተዋል።

አቶ አለማየሁ÷ ሕዝቦች በጋራ ክልል ለመመስረት ባነሱት ጥያቄ መሠረት መንግሥት ጥናት አስደርጎ የሕዝቦች የቆየ እሴትና መሠረታዊ መስተጋብር ሳይሸረሸር አብሮ የሚደራጁበት ሁኔታ እንዲፈጠር ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መደረጉን ተናግረዋል።

የዴሞክራሲያዊ ባህል ከፍ ብሎ ሁሉም ዜጎች ምክክር በማድረግና ተግባቦት ላይ በመድረስ ሕዝቦች በቀጥታ የሚሳተፉበት ሕዝበ ውሳኔ መሆኑን አስረድተዋል።

በሁሉም አከባቢዎች በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ ተመስርቶ ያለ አንዳች የፀጥታ ስጋት ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሰልፍ ድምፅ እየተሰጠ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ ÷ የፀጥታ ኃይሉም ሠላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ በጥብቅ እየተከታተለ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ በጌዴኦ ዞን የምርጫ ማስተባበሪያ ውስጥ በሚገኙ 626 የምርጫ ጣቢያዎች የህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጠት ተጀምሯል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ አበባው ታደሰ÷ በምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምጽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ አበባው ህዝቦች በጋራ በመሆን ክልል በመመሥረት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጥያቄያቸው የሚመለሥበት በመሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በወላይታ ዞንም በ1 ሺህ 112 የምርጫ ጣቢያዎች ከዛሬ ጠዋት ከ12 ሰዓት ጀምሮ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት እየተከናወነ ነው፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅኝት ባደረገባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ያነጋገርናቸው መራጮች ያለምንም ተፅዕኖ ድምጽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመለስ ታደለ፣ በኢብራሂም ባዲ እናበ ማቱሳላ ማቲዎስ

Exit mobile version