Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጓል – ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 
የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ም/ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እንደገለጹት ÷ የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ በሠላም እንዲከበር ከጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ጋር ዕቅድ በማዘጋጀት አስፈለጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡
 
በዚህ መሠረትም የጸጥታ አካላት እንግዶችን በምን መልኩ ማጀብ እና ጥበቃ ማድረግ በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ አስፈላጊውን የተግባር ልምምድ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
 
ጉባዔው እስኪጠናቀቅ ድረስ የእንግዶችን ሠላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሁሉም ዘርፍ አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
 
እንግዶች ከሚያርፉባቸው ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋርም በቅርበት እና በትብብር መሥራት የሚያስችል ትሥሥር መፈጠሩን ዳይሬክተሩ ለፋና ብድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
ማኅበረሰቡም በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ለእንግዶች ቅድሚያ በመስጠት እና ተገቢው ክብር በማሳየት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠቁመዋል፡፡
 
በተለይም እንግዶች በተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት መንገዶች ሊዘጉ ስለሚችሉ ተሽከርካሪዎች እና እግረኞች በትዕግስት እንዲጠብቁ አስገንዝበዋል፡፡
 
የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያጎላ ነው ያሉት ምክትል ኮማንደሩ÷የመዲናዋ ነዋሪዎች ጉባዔው በሠላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
 
ነዋሪዎች በየትኛውም ሁኔታ አጠራጣሪ ነገር ሲመለከቱም በአዲስ አበባ ፖሊስ ስልክ ቁጥር 011 111 0111 ወይም በ991 በመደወል ጥቆማ እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
Exit mobile version