Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የንግድ ምክር ቤት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ላይ እየተመከረ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድ ሥርዓቱን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የንግድ ምክር ቤት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡

የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶችን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/1995 ላይ የሚደረገውን ማሻሻያ በተመለከተ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ውይይት እየተደረገ ነው።

የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ ንግድና አምራች ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምቹና ቀልጣፋ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ የንግዱን ዘርፍ ለማዘመንና በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን በሯን ለዓለም አቀፍ ንግዱ ክፍት ማድረግ እንዳለባትም ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ መንግስት እና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት እንዲሠሩ ምኅዳሩን እንደሚያመቻችም አመላክተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ከተተገበረ እና ሁለቱ አካላት በቅንጅት ከሠሩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚያሥችልም ነው ያነሱት፡፡

የአባላቱን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ረቂቅ አዋጁ ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም አስገንዝበዋል፡፡

አምራቹን፣ ነጋዴውንና ሸማቹን ያቀፈ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር የግሉን የንግድ ዘርፍ ማጠናከር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

አዋጁ ለ20 ዓመታት በመቆየቱ የዓለምን ተለዋዋጭ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ማሻሻያ ማድረግ ማስፈለጉንም ነው የገለጹት፡፡

ማሻሻያው አምራቹን፣ ነጋዴውንና ሸማቹን ያቀፈ የንግድ ስርዓት ለመፍጠር አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

የግሉን ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግም በተናጠል ሳይሆን በቡድን ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የንግድ ቀጣና አባል መሆኗን እና የዓለም አቀፍ የንግድ ምክር ቤት አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧን አስታውሰዋል፡፡

Exit mobile version