Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጮቄ ተራራ ኢኮ ቱሪዝም ልማት የዓለም ድንቅ ቱሪዝም መንደር ውድድር አሸናፊ ሆነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው የጮቄ ተራራ ኢኮ ቱሪዝም ልማት የዓለም ድንቅ ቱሪዝም መንደር ውድድርን አሸንፏል፡፡
 
በተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የጮቄ ተራራ ኢኮ ቱሪዝም ልማት የዓለም ድንቅ ቱሪዝም መንደር ውድድር አሸናፊ አድርጎ መርጧል።
 
ሽልማቱን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ከጮቄ ሙሉ ኢኮ ሎጅ ተወካዮች ጋር በሳዑዲ ዓረቢያ አሉላ ከተማ ተቀብለዋል።
 
በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ50 በላይ ሀገራት እና ከ100 በላይ የቱሪዝም መዳረሻዎች መሳተፋቸውን ከቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ማህበረሰቡን ያሳተፉ እና ዘላቂ የሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መሸለሙን በመርሐ ግብሩ ላይ አስታውቋል፡፡
 
በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
 
የሙሉ ኢኮሎጅን እሳቤ መሰረት በማድረግ ማኅበረሰብን መሰረት ያደረገ ቱሪዝም፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ኢኮ ቱሪዝም እና ዘላቂ አካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረገ አኗኗርን የሚተገብርበት መንደር መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
 
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከፍተኛ ተራራዎች አንዱ የሆነው ጮቄ ተራራ ላይ የሚገኘው የቱሪዝም መንደር በዋናነት ለገጠር ልማት አንቀሳቃሽ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
Exit mobile version