አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ በኢትዮጵያ ከብራዚል አምባሳደር ጃንዲር ፌርራ እና ዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ከምግብና ስርዓተ-ምግብ ዳይሬክተር ሊናት ኑፊልድ ጋር ተወያዩ፡፡
ሚኒስትሩ ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ውይይት÷ የብራዚል መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር አሲዳማ አፈር እና የአፈር ለምነት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በሌላ በኩል የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ምግብና ስርዓተ-ምግብ ዳይሬክተር ሊናት ኑፊልድ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ እስካሁን እያደረገ ያለውን ጥረት ማድነቃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የምግብና ስርዓተ-ምግብን ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ለማሳካት ድርጅቱ በተለያየ መልኩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡
የምግብና ስርዓተ-ምግብ ዳይሬክተሯ ሊናት ኑፊልድ በበኩላቸው÷ የምግብና ስርዓተ-ምግብን ለማሻሻል የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካት እና የምግብ እና የስርዓተ-ምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ድርጅታቸው ሙያዊ እና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡