አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ወጪ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን ይፋ አደርጓል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሁለት የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ዙሪያ ያካሄደውን የዳሰሳ ጥናት አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አድርጓል።
ተቋሙ የዳሰሳ ጥናቱን ያካሄደው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እየተገነባ ያለውን የአጂማ ጫጫ የመስኖ ውሃ ፕሮጀክትና በወላይታ ዞን የወይቦ የመስኖ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም ውጤታማነትና የአሰራር ተጠያቂነት ላይ መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ እንዳለ ሃይሌ (ዶክተር)፥ የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ከውጤታማነትና ተጠያቂነት አንፃር ችግር እየተስተዋለባቸው ነው ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የፕሮጀክቶቹ የግንባታ ሂደት ለቅሬታ የሚዳርጉ አሰራሮችን የሚከተሉ፣ ግልጽነት የጎደላቸው መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም የዳሰሳ ጥናት የተደረገባቸው የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በተመደበላቸው በጀት የማይጠናቀቁ በመሆናቸው የውጤታማነትና ተጠያቂነት ችግር መታየቱን ጠቅሰዋል።
በሁለት ዓመትና በአምስት ዓመት እንዲጠናቀቁ የጊዜ ገደብና በጀት የተያዘላቸው ፕሮጀክቶች እስከ አስር ዓመት የሚቆዩበትና ከእጥፍ በላይ ፋይናንስ በመጠየቅ መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጉ እንደሚገኙ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።
በጥናቱ ውጤት መሰረት የአጂማ ጫጫ የተሻለ የአፈፃፀም ውጤታማነትና አሳታፊነት ቢኖረውም በወይቦ የመስኖ ግድብ ግን ሰፊ ችግር መኖሩን ገልጸዋል።
በተለይ የወይቦ ፕሮጀክቱ ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ አንፃር በአሁኑ ወቅት ከ50 በመቶ በላይ መድረስ ሲገባው 9 በመቶ ላይ ብቻ እንደሚገኝ ጠቅሰው ከመሬታቸው ከተነሱት 420 አርሶ አደሮች ውስጥ ካሣ ያገኙት 21 ብቻ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
የፕሮጀክቱ የአፈፃፀም ውጤታማነትና ያለው የተጠያቂነት አሰራር ደካማ መሆኑን በተደረገው ጥናት መለየቱን በመጥቀስም፥ ለፕሮጄክቶች ውጤታማነት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።