Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትና ከዋጋ ንረት ለመከላከል አማራጭ የገበያ ቦታዎች ተዘጋጁ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትና ከዋጋ ንረት ለመከላከል አማራጭ የገበያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ግብይት የሚፈፀምበት የቁም እንስሳት በሶስት አማራጮች እንደሚፈፀም ተናግረዋል።

በዚህም በአንድ ገበያ ሲካሄድ የነበረውን የበግ፣ የፍየል፣ የከብት፣ የዶሮና የእንቁላል ግብይትን ለየብቻ፣ በየመግቢያ በሮች ንዑስ ገበያ ማዘጋጀት እና የቤት ለቤት ሽያጭ ይኖራልም ነው ያሉት።

የከብት ቆዳ፣ የበግና ፍየል ሌጦ ግብይት እና የግብርና የኢንዱስትሪ ምርቶች ውጤቶች በሶስቱ አማራጮች ይካሄዳሉ ብለዋል ምክትል ሀላፊው።

በመንግሥት የሚቀርቡ ሸቀጦች ስኳርና ዘይትን ጨምሮ በየሰፈሩ በተመደቡ ነጋዴዎችና ህብረት ስራ ማህበር ግብይት ይፈፀማል ብለዋል።

ከመንግስት ዱቄት የሚወስዱ የመንግስት ሰራተኞችም በየመስሪያ ቤታቸው ርቀታቸውን ጠብቀው እንደሚረከቡ በመግለጫው አንስተዋል።

ይህ ግብይት በተገቢው ሁኔታ እንዲፈፀም ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የንግድ ግብረሀይል መኖሩን የገለፁት አቶ ተዋቸው ማህበረሰቡ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ያወጣቸውን የገበያ አማራጮች እንዲጠቀምና እንዲያከብር መልክት አስተላልፈዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version