Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በደቡብ ክልል ከ100 ሚሊየን በላይ የእንሰት ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት አመት የበልግ ወቅት 50 ሺህ 251 ሄክታር መሬት ላይ ከ100 ሚሊየን በላይ የእንሰት ችግኝ ለመትከል እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ነቢዩ ቤዛ፥ እንሰት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

1 ሚሊየን 5 ሺህ 28 የእንሰት ስር ቀበራ በመፈጸም ከዚህ የእንሰት ስር ከ100 ሚሊየን በላይ የእንሰት ችግኝ ለማግኘት ታቅዶ እየተባዛ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

በክልሉ 406 ሺህ 619 አርሶ አደሮች በእንሰት ተከላው ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የጌዴኦ ዞን ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ከ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ40 ሚሊየን በላይ የእንሰት ችግኝ ለመትከል እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት።

የወላይታ ዞንም እንዲሁ  ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፥  12 ሺህ 464 ሄክታር መሬት ላይ 24 ነጥብ 9 ሚሊየን የእንሰት ችግኝ አባዝቶ የአርሶ አደር ማሳ ላይ ለመትከል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

የጎፋ ዞንም በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 2 ሚሊየን የእንሰት ችግኝ ለመትከል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው፥ ሌሎችም ወደ እንሰት ችግኝ የማባዛት ተግባር መግባታቸውን ነው ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡

የበልግ ወቅት የእንሰት ችግኝ ለመትከል አመቺ መሆኑን የገለጹት አቶ ነቢዩ፥ እንሰት ለምግብነት፣ ቅጠሉ ደግሞ ለእንስሳት መኖነት እንደሚያገለግልም አስረድተዋል፡፡

በየሻምበል ምህረት

 

 

 

 

 

Exit mobile version