አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምሥት የብራይሌ ጎሳ አባላት ብቻ የሚነገረውን የኦንጎታ ቋንቋ ለትውልድ እንዲሻገር እየሰራ መሆኑን አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡
የአንጎታ ቋንቋ በደቡብ ክልል ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በሚገኙ ዕድሜያቸው ከ40 በላይ በሚሆናቸው÷ ጌዶ ቃውላ፣ ኦዳ ቆራዮ፣ ጉያዋ ቆራዮ፣ ጉምቦ ቃውላ፣ ጉምቦ ቃሮ በተባሉ ሦስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች ብቻ ይነገራል፡፡
ይህን የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት የኦንጎታ ቋንቋ ለማስቀጠል ከተናጋሪዎቹ ጋር በመተባበር መዝገበቃላት ለማዘጋጀት እና ወደ ትውልድ እንዲሻገር ጥናት እየተሠራ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ጥናቱ የቋንቋውን ቤተሰብ በሣይንሳዊ መንገድ ለመለየት እንደሚያስችል በዩኒቨርሲቲው የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር እና የጥናቱ ተሳታፊ ሰዒድ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ጥናቱ በቋንቋው ተናጋሪዎች ዘንድ ያሉ ትውፊቶች ፣ ታሪኮች፣ ተረቶች ፣ የባህል መድኃኒቶች፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ባህሎችን ለመሰብሰብ ብሎም ለመሠነድ ይረዳል ብለዋል፡፡
የቋንቋው ተናጋሪዎች ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን በተለያየ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ከ100 ዓመታት በፊት በተካሄደ ጥናት ቋንቋው 10 ሺህ ተናጋሪዎች እንደነበሩት እና በፈረንጆቹ 1940ዎቹ በተካሄደ ሌላ ጥናትም 5 ሺህ መድረሱን ሰዒድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ከፈረንጆቹ 1970 እስከ 1990ዎቹ በተሠሩ ጥናቶችም የኦንጎታ ቋንቋ ተናጋሪዎች 89 መሆናቸው እና በፈረንጆቹ 2006 በተካሄደ ጥናት ስምንት ብቻ መቅረታቸውን ጥናቶቹን ጠቅሰው ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ከወራት በፊት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጉዳዩ ላይ የሠራውን ፕሮግራም ይመልከቱ፡- https://www.youtube.com/watch?v=elb2CJ6BS2g
በዓለማየሁ ገረመው