Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በቂ የድጋፍ ዓይን ያላየው የቡርጂ ልዩ ወረዳ ድርቅ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ቡርጅ ልዩ ወረዳ በድርቅ ምክንያት ለችግር ለተዳረጉ ወገኖች በቂ ድጋፍ እየቀረበ አለመሆኑን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ፡፡
 
ድርቁ በሰው እና እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን እስካሁን፥ ከ1 ሚሊየን በላይ እንስሳት መሞታቸው ተገልጿል፡፡
 
የቡርጂ ልዩ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቤል ሃይላ እንዳሉት÷ በልዩ ወረዳው ከ83 ሺህ 528 በላይ ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል፡፡
 
የክልሉ መንግሥት እስካሁን 2 ሺህ 400 ኩንታል በቆሎ እና አልሚ ምግቦችን ድጋፍ ቢያደርግም ከተጋላጮች ቁጥር አንጻር በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
በሌላ በኩል የኮንሶ ዞን 200 ኩንታል ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
 
የቀረቡት ድጋፎች ለደከሙ 26 ሺህ 743 ሰዎች ብቻ ተደራሽ መሆኑን ገልጸው ይህም በተቆራረጠ ጊዜ ስለሆነ እየደረሰ ያለው ጉዳቱን ማስቀረት እንዳልቻለ ጠቅሰዋል፡፡
 
ድርቁ በእንስሳት እና በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው÷ በማንኛውም የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ክልሎች በደብዳቤ ሲጠይቁ የፌደራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
 
ከዚያ በኋላ ያለው የሥርጭት ሥራ የሚከናወነው በክልሎች መሆኑን አመላክተዋል።
 
በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጠን የክልሉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንን ለማናገር ያደረግነው ሙከራ ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም።
 
በዮሐንስ ደርበው
Exit mobile version