አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ ተዋጊዎች የመልሶ ማቋቋም ብሄራዊ ፕሮግራም መነሻ ሐሳብ ላይ በአሶሰሳ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ይሳቅ አብዱልቃድርን ጨምሮ የተለያዩ የክልልና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
አቶ አሻድሊ ሀሰን ባደረጉት ንግግር÷ እንደ ክልል ከነበርንበት ችግር ለመውጣት ከታጣቂዎች ጋር በሰላም በመነጋገር የትጥቅ ትግል አቁመው እንዲገቡ አድርገናል ብለዋል፡፡
እነዚህን ታጣቂዎችም ሆነ ለሀገራቸው ሲሉ ሲዋደቁ ለነበሩ የቀድሞ ተዋጊዎች ለማቋቋም የተጀመረው ስራ ክልሉ ሲጠብቀው የነበረ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የምንረባረብበት ይሆናል ነው ያሉት፡፡
አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ዋና አላማ ለሀገርና ህዝብ ሲሉ ብሄራዊ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ እና ኢትዮጵያ ባጋጠማት ጦርነቶች ዋጋ የከፈሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን ራሳቸውንና ሀገራቸውን ሊጠቅሙ በሚችሉበት ደረጃ መልሶ በማቋቋም ወደ ልማት ማስገባት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ማቋቋም የሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ትልቅ ዋጋ አለው ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የክልሎች ድርሻ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ በቁርጠኝነት እና በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል፡፡
ውይይቱ በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች የጋራ መግባባት የሚያዝበትና የስራ አቅጣጫዎች የሚሰጡበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡