አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የተመራው ልዑክ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ዱባይ ከተማ የሚገኘውን ዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ ጎብኝቷል።
ልዑኩ ከጉብኝቱ ባሻገር ከፓርኩ ኢንተርናሽናል ኮመርሻል ማናጀር ሳሊም አል ሀጀሪ ጋር በኢንቨትመንት ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል፡፡
የዱባይ ኢንቨስትመንት ማናጀር ሳሊም ተቋማቸው በኢትዮጵያ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኩ የማምረቻ ስፍራዎችን፣ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን እንዲሁም የአስተዳደር ህንፃዎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ስፍራዎችን ያካተተ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም ከዱባይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በበይነ መረብ ግንኙነቶችን ሲያደርግ እንደቆየ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ ዱባይ ላይ ከሚገኙ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ሲሆን፥ 2 ሺህ 300 ሄክታር ላይ ያረፈ እና ከ8 ሺህ በላይ ሰራተኞችን የሚያንቀሳቅስ ፓርክ ነው።