አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 9 ወራት በአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹ አሰራር በፈጸሙ ከ12 ሺህ በላይ የመንግስት አመራሮችና ሰራተኞች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው በሰው ሃብትና መልካም አስተዳድር ዘርፍ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከተገልጋዮች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የመልካም አስተዳደር ችግር በስፋት ከሚስተዋልባቸው ተቋማት መካከል ደንብ ማስከበር ባለስልጣን፣ ፍትህ ቢሮ፣ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ግዥና ንብረት አስተዳደርና መሬት አስተዳደር ቀዳ ሚዎቹ መሆናቸው ተጠቅሷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቢስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ ኤፍሬም ግዛው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በተቋማት የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
ከህብረተሰቡ በሚሰጡ ጥቆማዎች መሰረትም ኃላፊነታቸውን በቅጡ ከመወጣት ይልቅ በብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል ነው ያሉት።
በቢሮው የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ አበበ ÷ ባለፉት 9 ወራት በ46 ተቋማት ውስጥ ሙስናን ጨምሮ በብልሹ አሰራር የተዘፈቁ ከወረዳ እስከ ማዕከል ባሉ ከ12 ሺህ 500 በላይ አመራርና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
እርምጃው ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ስራ ማባረር የሚደርስ መሆኑን ገልፀው÷ እርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ በወረዳ 1 ሺህ 490፣ በክፍለ ከተማ 10 ሺህ 43 እንዲሁም በማዕከል 1 ሺህ 54 መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በሚፈጥሩ አመራርና ሰራተኞች ላይ ተጠያቂነትን የማስፈን ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በየዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹና የተንዛዙ አሰራሮችን ለማስቀረት ችግሮችን ለይቶ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በመዘርጋት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሁንም እንዳልተቀረፉ ገልጸው÷ በተለይም በፀጥታ እና በትራንስፖርት ዘርፎች ህብረተሰቡን ለዘረፋ፣ ሌብነት የሚዳርጉ እና ኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲሰጥና ያለምንም ክፍያ አገልግሎት የማግኘት መብቱን እንዲያስከብር መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡