አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሁቱ እና ቱተሲ ጎሳዎች እርስ በእርስ የተገዳደሉበት የሩዋንዳው የዘር ፍጅት 29ኛ አመት መታሳቢያ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
በመታሰቢያ ስነ ሰርዓቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ÷ አንድ ሚሊየን ዜጎችን የቀጠፈው የዘር ፍጅት የአፍሪካውያን አሳዛኝ ታሪክ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሩዋንዳውያንን ከስተት ስናስብም በአፍሪካ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚፈፀሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ለመከላከል ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት በማሳየት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከል ከአፍሪካ ህብረት፣ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ከሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በበኩላቸው÷ መታሰቢያው ለሩዋንዳ ወንድም እና እህቶቻችን ያለንን አጋርነት የምናሳይበት እና ለአህገራችን ሰላም እና ደህንነት የምንሰራበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሩዋንዳ አምባሳደር ሆፕ ቱሙኩንዴ ጋሳቱራ÷ በመታሰቢያው የተገኙትን በማመስገን ሁሉም ከሩዋንዳውያን አሳዛኝ ታሪክ ትምህርት ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡