አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 2 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በስሎቬኒያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ÷ኢትዮጵያ በቱሪዝም፣ በአገልግሎት እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላትን ያልተነካ እምቅ አቅም በመጠቀም የሁለቱን ሀገራት ሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ ገልጸዋል፡፡
ላለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ ዘርፍ በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ስሎቬኒያ በቴክኖሎጅ፣ በጥናትና ምርምር እና በኬሚካል ኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ለማሳደግ ይሰራልም ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
የስሎቬኒያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ጉዳዮች ሚኒስትር ታኒያ ፋየን በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ ቆይታችን የጋራ የሚያደርጉንን እድሎች በመጎብኘትና በመረዳት በቀጣይ ሁለትዮሽ ግንኙነትን በሚያሳድጉ እና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ሁሉ አብረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸውና አዳዲስ እየተገነቡ ስላሉ የቱሪስት መዳረሻዎችም ለልኡካኑ ማብራሪያ መሰጠቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

