Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ድርቅና ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ህፃናት ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ተወካይ አቡበከር ካምፓ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ልማት ላይ ቁልፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተው÷ በተለይ በህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እና ትምህርት እንዲዳረስ እየተገበራቸው ያሉ መርሐ ግብሮችን አድንቀዋል።

ዩኒሴፍ ድርቅ እና ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ህፃናት ትኩረት መስጠት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል ፡፡

ድርጅቱ በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ ህፃናት የሚያደርጋቸውን የሰብዓዊ ድጋፎች እና የልማት ስራዎች ይበልጥ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

አቶ ደመቀ በፕሪቶሪያ ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት አተገባበር ለተወካዩ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን÷ መንግስት በሙሉ ቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አቡበከር ካምፓ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ መሆኑን አንስተዋል።

የሰላም ስምምነቱ አተገባበር ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ እና ድጋፍ ለሚሹ ህፃናት የሰብዓዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግ የተሻለ ሁኔታ መፍጠሩን ነው የገለጹት፡፡

ዩኒሴፍ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በህፃናት ላይ ከሚያከናውናቸው የልማት እና የተራዕዶ ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ የተናገሩት ተወካዩ ÷ዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ሁነኛ የልማት አጋር ሆኖ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

Exit mobile version