አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 4 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 253ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህም መሠረት ከ5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 82 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቀርበው በምክር ቤቱ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።
ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ 55ቱ በግብርና፣ 15ቱ በኢንዱስትሪ እና 12ቱ ደግሞ በአገልግሎት ዘርፎች መሆናቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ፕሮጀክቶቹ ከ4 ሺህ በላይ በቋሚነት እና ከ8 ሺህ በላይ በጊዜያዊነት በአጠቃላይ ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በፊት በመስተዳድር ምክር ቤቱ ውሳኔ ተሰጥቶባቸው መሬት በምደባ የወሰዱ አልሚዎች በታለመለት መልኩ ወደ ተግባር ስለመግባታቸው እና በየአካባቢው የሚፈለገውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ለውጥ ስለማምጣታቸው በየደረጃው በሚገኙ አስተዳደር አካላት ተገቢው ክትትል እና ድጋፍ እንዲደረግ መስተዳድር ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በሌላ መልኩ መስተዳድር ምክር ቤቱ የቀረበለትን ደንብ እና ሌሎች አጀንዳዎች መርምሮ አፅድቋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

