Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ለበዓላቱ የሚያስፈልጉ የፍጆታ እቃዎች በስፋት እየቀረቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመጪዎቹ በዓላት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ እንደገለጹት፥ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች 110 በላይ የሚሆኑ የእሑድና ቅዳሜ ገበያዎችን በማዘጋጀት የግብር እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች ለማህበረሰቡ እየቀረቡ ነው፡፡

በክልሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት እና ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ለመጪዎቹ የትንሳኤ እና ዒድ አልፈጥር በዓላት ለገበያ መቅረቡንም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ለበዓላቱ ከ500 ሺህ በላይ የቀንድ ከብቶች፣ 5 ሚሊየን ፍየል እና በግ እንዲሁም ከ10 ሚሊየን በላይ ዶሮዎች በማህበራት በኩል ለገበያ እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል፡፡

ምርቶቹ በተቀላጠፈ እና በተሳለጠ ሁኔታ ለገበያ እንዲቀርቡም ኬላዎች እንዲነሱ መደረጉን ምክትል ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በበኩሉ፥ በመዲናዋ በሚገኙ የተለያዩ የገበያ ቦታዎችማ ባዛሮች ለበዓላቱ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡመሆኑን አስታውቋል፡፡

ለዚህም ከክልሎች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱ ነው የተገለጸው፡፡

በዘይት፣ ስኳር ፣ስንዴ ዱቄት፣ ጤፍ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ሊከሰት የሚችልን እጥረትና የዋጋ ንረት ለመቅረፍም ምርቶቹ በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ መደረጉ ተመላክቷል፡፡

በዚህ መሰረት 23 ሺህ ኩንታል የሚደርስ ጤፍ እንዲሁም 7 ሺህ በግ እና ፍየል በማህበራቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

የመጪዎቹን በዓላት ምክንያት በማድግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ምርት በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version