Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሱዳን ወንድማማች ፓርቲዎች ከግጭት አባባሽ ድርጊቶች ተቆጥበው ወደ ሰላም ንግግር እንዲመለሡ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሱዳን ወንድማማች ፓርቲዎች ከግጭት አባባሽ ድርጊቶች ተቆጥበው የተፈጠረውን ግጭት በውይይት እዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዳዩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ  ሃይሎች(ልዩ ሃይሎች) መካከል በመዲናዋ በካርቱም እና በሌሎች የሱዳን ከተሞች የተፈጠረውን ግጭት በከፍተኛ ስጋት እየተከታተለ ይገኛል ብለዋል።

ለሱዳን ህዝብ እና መንግሥት የሚኖረንን ስጋት የሚያሳድገው እነዚህ ግጭቶች የሱዳንን ጥንታዊ ሥርዓቶችና እሴቶች የሚቃረኑ በመሆናቸው እና ብሎም የሱዳን ሕዝብ ለበጎ ሥራ በሚተጋበት እና ወደ ፈጣሪ ለመቃረብ በሚማስንበት በዚህ በተከበረው የረመዳን ወር የመጨረሻ ቀናት ላይ በመሆኑ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ስለሆነም ሁሉም ወገኖች እንዲታገሡ፣ ትግሉ እንዲቆም፣ ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ እና ለወንድማማች ሱዳን የበላይ ጥቅም ሲባል  የድርድርና የመግባቢያ መንገድን እንዲመርጡ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“የአህጉራዊ ድርጅታችን ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኝበት የመዲናችን የአዲስ አበባ በሮች ክፍት እንደሆኑ በሱዳን ላሉ ወንድሞቻችን ጥሪ እናቀርባለንም” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፓርቲዎቹ ከግጭቱ በፊት የጀመሩትን ውይይት እና የሰላማዊ ድርድር መንገድ እንዲያጠናቅቁም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ የወንድማማችነት እና የጉርብትና ግዴታዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ጠቁመው÷ ፓርቲዎቹ ሁኔታውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ  እና የጠመንጃ እና የጥይት ድምጽ ዝም እንዲል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“በመሀከላችሁ ገብተን እንደወንድምነታችን እናሸማግላችሁ ዘንድ ጥሪ ብታቀርቡልን፤ ያለምንም ማመንታት በተቻለው ፍጥነት ወደ ካርቱም በመምጣት ግዴታችንን እንወጣለን” ሲሉም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ÷ በብዙ ጦርነቶች ለተንገላታውና የጦርነት ስቃይ ገፈት ቀማሽ ለሆነው የሱዳን ህዝብ ሲባል ግጭቱን በሰላማዊ ውይይት እና ድርድር እንዲፈቱም ጠይቀዋል፡፡

 

 

 

 

Exit mobile version