አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የመከላከያ ሠራዊቱንና የሠራዊቱን አመራሮች ስም የሚያጎድፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አሳሰበ፡፡
የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ÷ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ አንዳንድ አካላት ሆን ብለውና በተቀናጀ አግባብ በሀሰተኛ መረጃ የመከላከያ ሰራዊትን እና የአመራሮቹን ስም እያጎደፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የእነዚህ ቡድኖች ዓላማ የሠራዊቱን ስም በማጥፋትና በሀሰት በመፈረጅ እርስ በርሱ እንዳይተማመን ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው÷ይህም ፈጽሞ ሊሳካ የማይችል እኩይ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በሠራዊቱ እና መሪዎቹ መካከል ያለውን ጠንካራ የዕዝ ሰንሰለት ለማላላት የጥፋት አጀንዳ እንደሚፈጥሩ የተናገሩት ኮሎኔል ጌትነት÷የዚህ ተልዕኮ ዋነኛ ዓላማም ሀገር ማፍረስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በአንድ እጅ ትጥቅ በሌላ እጅ ደግሞ ፖለቲካ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት።
ህብረተሰቡ የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊትን ለመከፋፈል የሚጥሩ አካላት መኖራቸውን ተገንዝቦ÷ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር ዝግጁ መሆኑን መግጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

